ዲዮገንስ ውሻው ፤ አስገራሚ የጥበብ ህይት

ታሌስ ላይ በሚጀምረው የጥንታዊ ግሪክ ፍልስፈና ታሪክ ከአርስቶትል ሞት በኋላ  ገነው ከወጡ የፍልስፍና ዘዉጎች መካከል  የሲኒስዝም ፍልስፍና አንዱ ሲሆን የዚህ ፍልስፍና ፈላስፋዎች ሕይወትን እንደወረደ ተፈጥሯዊ በሆነ መልኩ መኖር እንደሚገባ የሚያስተምሩ አኗኗራቸውም ከማህበረሰቡ የመገለልና ራስን ነፃ አድርጎ ቀለል ያለ ህይወት በመምራ ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ ፡ በዚህ የፍልስፍና ጊዚያት የታላቁ እሰክንድር የመስፋፋት ዘመቻ ተከትሎ የግሪክ ፍልስፍና ከሌሎች ማህበረሰብ ፍልስፈናዎች ጋር እራሱን እየደባለቀ የመጣበት ሁኔታ ነበር፡፡ በዚህ ጊዚያት ከተነሱ ፈላስፋዎች መካከል ዲዮጋንስ ውሻው የሚባለው አስገራሚ የጥበብ ሕይውት ያለው ሰው ነበር፡፡


አጅግ በጣም ለየት ያለ ከሌላው ማህበረብ የተገለለ ኑሮ ይኖር የነበረው ዲዮጋንስ ሲኒሲዝም የሚባለው የፍልስፍና አስተምህሮት የራሱን ተለየ ባህሪ እንዲይዝ ያደረገ ሰው ነበር፡፡ ዲዮገንስ ትውልዱ የአሁኗ ቱርክ ሲሆን በግዞት ወደ ግሪክ እንደመጣ ይነገራል፡፡  አንድ ሰው ወደ ግሪክ በግዞት ተሰዶ እንደመጣ ሲተቸው “እናንተ ስለገፋችሁኝ ፈላስፋ ሆንኩኝ” ብሎ መልሶለታል ይባላል፡፡ ያም ሆኖ “የአለም ዜጋ” የመሆን ስሜት በተለምዶ ኮስሞፖለቲያን የሚባለውን አለም አቀፋዊነት የዜግነት ስሜት ዲዮገንስ ለስቶይኮች እንዳስተዋወቀ ይነገራል፡፡ በአስተሳሰብና በባህሪ የሶቅራጥስን አምሳያ ገፅታን ቢይዝም በጣም የገነኑ ባህሪያቱ “ያበደው ሶቅራጥስ” እንዲባል አስችሎታል፡፡ ዲዮገንስ በአቴንስ ህይወቱ ከሶቅራጥስ ተማሪ የነበረው እና አንቴስትነስ ጋር እንደ ተማሪ ሆኖ አብሮ ይኖር እንደነበረ ይነገራል፡፡ በአንድ ወቅት አንቴስትነስ በዲዮገንስ ተበሳጭቶ ወደምትፈልግበት ሂድ ብሎ ዱላ አንስቶ ሊመታው ሲል ዱላውን አናቱ አደርጎ “ ምታኝ፡፡ አንተ ከምትናገው ንግግር ውጪ እኔን ሊያባርረኝ የሚችል ጠንካራ ብትር የለም” ካለው ጊዜ ጀምሮ ተማሪው ሆኖ እንደቆየ ተፅፏል፡፡

የዲዮገንስ ፍልስፍና እኛ ነቆራ እና ፉገራ የምንለው አይነት ቢሆንም ቁምነግር ያዘለና በውስጡ ጥልቅ ፅንሰ አሳቦችን የያዙ አሳቦችን በድንገት የማፍለቅ ችሎታ ነበረው፡፡ ዲዮገንስ በወቅቱ ያለውን የአኗኗር ባህል ስለሚጥስ እብድ የሚል መጠሪያ ተሰጥቶት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ዲዮገንስ በፊናው ባህል ራሱ ምክንያታዊነትን የሚጥስ እብደት ነው በሚል አጣጥሎታል፡፡ “ ብዙሀኑ በጣት ብቻ ስሜቱ የሚዘበራረቅ እብድ ነው” የሚለው ዲዮገንስ “ የመሀል ጣትህን ካወጣህ እብድ እንደሆንክ ይሰማቸዋል፡፡ ትንሷን ጣትህን ስታወጣ ግን ምንም አይሰማቸውም”  እንደ ዲዮገንስ እምነት ብዙሀኑ የሚኖረው በትክክለኛ ምክንያት ሳይሆን በሚሰማው የተዛባ ስሜት ነው፡፡ የዲዮገንስ ፍልስፍና ከተደራጀ የማህበረሰብ መዋቅር በአካልም በስሜትም ተለይቶ በመዉጣት ፍልስፍናውን ራሱ በመኖር የሚያስተምርበት ገጽታ ነበረው፡፡ ለዲዮገንስ ንብረት የማፍራት እና  የኔ ነው የእኛ የሚል የባለቤትነት ስሜት የሚባል ስሜት የለም፡፡ ሀፍረት፣ ኩራት፣ ባህል ወግ የሚባሉት ማህበራዊ የሰው ልጅ መለኪያዎች በዲዮገንስ ዘንድ ዋጋ የላቸውም፡፡ በዚህ የተነሳ ዲዮገንስ በአስተሳሰቡ እጅግ ረቂቅና ምጡቅ ቢሆንም ብዙ ህይወቱን ከማህበረሰቡ ሞራል ዉጪ በመሆን ይኖር የነበረ ሲሆን ምግብ ከመመገብ አንስቶ አብዛኛውን የሕይወቱን የእለት ተዕለት እንቅስቃሴውን ሆነ ብሎ ሰው በብዛት በሚሰበሰብባቸው የገበያና የመሳሰሉት ቦታዎች ያደርግ ነበር፡፡  አንድ ጊዜ ዲዮገንስ በገበያ ቦታ ቁርሱን ሲበላ “በገበያ ቦታ  ቁርስ መብላት ነውር አይደለምን??” ብሎ ለጠየቀው ዲዮገንስ ሲመልስ “ቁርስ መብላት ከቦታ ጋር የሚያገናኘው ነገር ከሌለ በገበያ ቦታ ቁርስ መብላትም  ከቦታው ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም” ሲል መልሶለታል፡፡  አሳቡ እንደገባኝ ለድርጊቱ ቦታ ሰይመን የሰጠነው እኛ ነን እንጂ የድርጊቱ ባህሪ ከቦታ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ለማለት ሳይሆን አይቀርም፡፡ በሌላ ንግግር ዲዮገንስ “ ባዶ ሆድን በመፈተግ ረሀብን ማስታገስ ቢቻል እንዴት ጥሩ ነበር” ሲል ተናግሯል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ በገበያ መሀል በአደባባይ ሲበላ ያዩት “ውሻ! ውሻ! “ ብለው ሲጮሁበት ” ውሻስ እናንተ ናችሁ፡፡ እኔ ጌታችሁ ስበላ ቆማችሁ የምትቁለጨለጩ” ብሏቸዋል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ የመንደር ኩታራዎች ከበዉት “ውሻው ውሻው ትነክሰናለህ?” ሲሉት “አትፍሩ! ውሻው የከብት ስጋ አይበላም፡፡ “ ብሎ መልሶላቸዋል፡፡ አሳቡ እናተ ከብት ናችሁ እንደ ማለት ነው፡፡

image

ዲዮገንስ አኗኗሩ ቀላል ፣ የራሱ መኖሪያ ቤት የሌለው እና በአቴንስ ጎዳናዎች ላይ በመዘዋወር በልመና የሚኖር ሰው ነበር፡፡ የሚተኛው አቴንስ ጎዳናዎች ላይ ነበር፡፡ መኖሪያ ቤቱ አነስተኛ የበርሜል ጉማጅ ሆኖ ከቦታ ወደ ቦታ ሲዘዋወር ተሸክሞ ነበር የሚጓጓዘው ፡፡ የአቴናውያን ነዋሪዎች አመፅ በተቀላቀለበት የዲዮገንስ ድርጊት የሚበሳጩ ቢሆንም ለዲዮገንስ ከፍተኛ ፍቅርና አክብሮት ነበራቸው፡፡ የዲዮገንስን መኖሪያ በርሜል ልጆች ሲሰርቁበት ትልለቆቹ እንደሚያስመልሱለትና ዲዮገንስን እንደሚንከባከቡት ይነገራል፡፡ ይሁን የዲዮገንስ ምላሽ ምስጋና ሳይሆን ነቆራ እና  አብዛኛውን አቴናውያንን ስላላቸው የአኗኗር ዘይቤና እና የሞራል ልምምድ መተቸት የሚቀናው ሰው ነበር፡፡ በሚሰጣቸው ድንገተኛ መልሶች በጣም የሚገርም የማሰብ ብቃት ያለው ሰው እንደነበር ይነገራል፡፡ ሙዚቃና ቲያትር ጠቃሚ ያልሆኑ አድርጎ የሚመለከተው ዲዮገንስ ዉሻው ዘመናዊ አስተሳሰቦችና በተለይም የሰው ልጅ ስልጣኔ የፈጠረው ሕይወት የሞራል መዛባትን የሚያመጣ ችግር እንደሆነ አድርጎ የሚያምን ሰው ነበር፡፡በዚህ አሳብ ያልተስማማ  አንድ ሰው ዲዮጋንስ እውቀት ሳይኖረው ነው ፈላስፋ ነኝ የሚለው ሲል ሲተቸው ”ጥበበን ማስመሰል ከቻልኩ ፍልስፍና ማለት እሱ ነው ” ሲል መልሶለታል ይባላል፡፡

image

እንግዳና ያልተለመዱ ድርጊቶችን ሲፈፅም የሚታየው ዲዮጋንስ በአንድ ወቅት  በጠራራ ፀሐይ ሻማ ይዞ ሲዞር የተመለከተ ሰው በጠራራ ፀሐይ ሻማ ይዞ ለምን እንደሚዞር ሲጠይቀው “ሰው እየፈለኩ ነው” ብሎ እንደመለሰ ይነገራል፡፡ አሳቡ ትክክለኛ ሰውነተቻውን የሚኖሩት ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው የሚል ይዘት የነበረው እና ትክክለኛ ማንነነት በገሀድ የሚታየው እንዳልሆነ ለማመላከት ነበር፡፡ በሌላ ጊዜ ከዚህ አሳብ ጋር የሚመሳሰል ሌላ አጋጣሚ ደግሞ ዲዮገንስ የኦሎምፒክ ጨዋታ አይቶ ሲመለስ አንድ ሰው “ብዙ ተመልካቾች ነበሩ ወይ?` ብሎ ሲጠይቀው  “አዎ! ብዙ ተመልካቾች እና ጥቂት ሰዎች ነበሩ ፡፡” ሲል መልሶለታል፡፡ የዲዮገንስ የሞራል ፍልስፍና መተክል የቅንጦትትን ሕይወትን በመናቅ ቀለል ያለ ህይወት በመኖር የሕይወትን ዋጋ መቀነስ ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡  ዲዮገንስ “ ትልቅ ዋጋ ያላቸው በርካሽ ይሸጣሉ ፣ ለትንሽ ዋጋ ያላቸው በውድ ይሸጣሉ “ የሚል ፍልስፈና ነበረው፡፡ አንድ ጊዜ በጣም ታዋቂ የጦር ጄኔራል ዲዮገንስን እቤቱ እራት አብሮት እንዲበላ ሲጠይቀው “ ከአንተ ጋር በቅንጦት እራት ከምበላ በአቴንስ አደባባይ ላይ ጨው በልስ ይሻለኛል” እንዳለው ይነገራል፡፡ ለዲዮገንስ የቅንጦት ሕይወት የሰው ልጅ ነፃነትን ይገድባል፡፡ በዚህም ዲዮገንስ” ለነፃነቴ ስል ቅንጦት ሕይወት አልኖርም” የሚል እምንት ነበረው፡፡

ለምንም ነገር ደንታ የሌለው ዲዮገንስ ከታላቁ እክንድር ጋር ይገናኝና እስክንድር “ታላቁ እስክንድር እባላለሁ” ብሎ ሊተዋወቀው ሲል ዲዮጋንስም መልሶ “እኔ ደግሞ ዲዮገንስ ውሻው እባላለሁ” ብሎታል፡: በሌላ የእስክንድር አጋጣሚው ደግሞ ንጉስ እስክንድር “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” ብሎ ሲጠይቀው ወደ ላይ ቀና ብሎ “ እባክህ ፀሀዩዋን አትከለልኝ ፡፡ ልሙቅበት” እንዳለው ይነገራል፡፡ ታላቁ እስክንድርም በዲዮገንስ ማንነት በጣም ተገርሞ “ እኔ ታላቁን እስክንድር ሆኜ ባፈጠር ኖሮ ዲዮገንስን ብሆን እመኝ ነበር” ሲል ዲዮገንስም ቀበል አደረገና “ እኔ ደግሞ ታላቁ አሌክሳንደር ሆኜ ባፈጠር ኖሮ ዲዮገንስን ብሆን እመኝ ነበር” ብሎትልቁን ንጉስ እንደነቆረው ተፅፏል፡፡ በሌላ  ጊዜ ደግሞ ታላቁ እስክንደር ዲዮገንስን የሰው አጥንት ቁራጭ እያየ አገኘው፡፡ ታላቁ እስክንድርን ያየው ዲዮገንስም ዞር አለና “ የአባትህን አጥንቶች እየፈለኩ ነበር፡፡ ነገር ግን የትኞቹ አጥንቶች የባሪያ እንደሆኑ መለየት አልቻልኩም፡፡” ብሎ እንደተናገረ ይነገራል፡፡

አቴናውያን ስለ ዲዮገንስ ያላቸው ስሜት ፍቅር ከጥላቻ ጋር የተደባለቀበት ስሜት ነበር፡፡ በአንድ በኩል ዲገንስ የሚያገጥመውን የአሳብ ክርክር በብቃት ይገጥም ይገጥም ስለነበር በሚያነሳው አሳብ ሲገረሙ በሌላ በኩል በሚያደርገው ያልተለመደ ድርጊት እንደ እብድ ይመለከቱት ነበር፡፡ ዲዮገንስ አወቀውም አላወቀው  ያየውን  ሰው ሁሉ ከመናቆር የማይመለስ የሚያገኘውን ሰው በመቀለድ የሚያስተምር ፈላስፋ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ችሎታ የሌለው ሰው ክራር የሚመሰል ሙዚቃ መሳሪ ሲጫወት ያየውና “የተዘበራረቀ ሕይወትህን ማስተካከል ያቀተህ የተስተካከለ ድምጽን እንጨት ላይ ለመደርደር ስትሞክር አታፍርምን ?” እንዳለው ይነገራል፡፡

ዲዮገንስ ውሻ የሚለውን ቅጥያ እንዴት እንዳገኘው የተለያዩ አስተያየቶች አሉ፡፡ ራሱ ዲዮገንስ ሰዎች ውሻ ብለው ለምን ሊጠሩት እንደቻሉ ተጠይቆ ሲመልስ “ማንኛውንም ነገር ለሚሰጡኝ ጋር በፍቅር እጠጋለሁ፡፡ በሚከለክሉኝ ላይ እጮሃለሁ፡፡ ባለጌዎችን ደግሞ እናከሳለሁ” እንዳለ ይነገራል፡፡ ዲዮገንስ ሰዎች በተፈጥሮ ያላቸውን መልካምነት የቀየሩ ብልሹ ፍጥረታት እንደሆኑ ያምን ነበር፡፡ ሰዎች መልካምነትን ከዉሻ መማር አለባቸው ብሎ የሚያምነው ዲዮገንስ ውሻ በራሱ ስሜት የሚመራ ፣ ግልፅ ታማኝ እና እውነተኛ ፍጥረት አድርጎ ያስብ ነበር፡፡ ዲዮገንስ “ ሌሎቹ ዉሾ ጠላቶቻቸውን ለመጉዳት ይናከሳሉ፡፡ እኔ ደግሞ የምውደውን ለማስተማር የምናከስ ዉሻ ነኝ” ይል ነበር፡፡ ዲዮገንስ ውሻ የሚለውን ስድብ በፀጋ በመቀበል መልሶ ለአቴናውያን አስገራሚ ምላሽ ይሰጣቸው ነበር፡፡ ፕላቶ በሕይወት በነበረበት ወቅት ከዲዮገንስ ጋር እንደተገናኙ የነገራል፡፡ ፕሌቶ  ዛሬ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ በሚኖርበት ማህበረሰብ ጭምር በጣም የተከበረ ሙሁር ቢሆንም ከዲዮገንስ ስላቅ አላመለጠም፡፡ አንድ ጊዜ ፕሌቶ ውድ የሆነ የወይራ ዘይት ለመግዛት እያገላበጠ ሲመለከት ዲዮገንስ አየውና “ እንዴ ሙሁሩ! ደስታን ፍለጋ የሲሲሊ ባህርን ተሸግረህ ከምትመጣ ደስታህን ከጀርባህ ጥለኸው እንደመጣህ ብታውቅ አይሻልም ነበር?” ብሎታል፡፡  ፕሌቶም ሲመልስ “ እዛ እያለሁም በወይራ ዘይት እደሰት ነበር” ሲለው ዲዮገንስ ቀበል አደረገና “ እና ባህር ተሸግረህ እዚህ ምን አመጣህ ? የመጣህበት አገር የወይራ ዘይት የለም?” ሲል ጠይቆታል፡፡  ፕሌቶ ዲዮገንስን እንደ አውቆ አበድ ስለሚመለከተው በተደጋጋሚ ይገስፀው ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ፕሌቶ ዲዮገንስን “ውሻው” ብሎ ሲጠራው “አዎ! ለሚገዙኝ ብቻ ሳይሆን ለሚሸጡኝም ታማኝ የሆንኩ ውሻ ነኝ” ብሎታል፡፡

ዲዮገንስ በአንድ ወቅት በጀልባ ሲሄድ የባህር ወንበዴዎች ይዙትና በባርነት ይሸጣል፡፡ የሚያሻሻጥው የባሪያ ደለላ “ይህ ሰው ምን ይችላል?” ብሎ ሲጠይቅ ዲዮጋንስም ዞር ብሎ “ሰዎችን መግዛት ” ብሎ ከመለሰ በኋላ አጠገቡ ሊገዛው ይጠባበቅ ወደነበረ ጌታ በጣቱ እየጠቆመ “ ለዛ ሰው ሽጠኝ፡፡ ያ ሰው የሚገዛው ጌታ ይፈልጋል” ብሎ መለሰ፡፡ ያም ሰው በባርንት ዲዮጋንስን ገዛውና የንግዱ አስተዳዳሪ እና የልጁ አስተማሪ እንዲሆን እንዳደረገው ይነገራል፡፡ አይደለም ለሞቱ ለህይወቱም ብዙም ደንታ የሌለው ዲዮገንስ “በሞትክ ጊዜ ከቅጥሩ አስወጥተን ሬሳህን ለአዉሬዎች ብናስበላው ምን ይሰማሀል” ብለው ለጠየቁት ሲመልስ “ ብትር ከሰጣችሁኝ አዉሬዎቹን አባርራቸዋለሁ፡፡” አላቸው እነሱም ተገርመው “ በሞትክ ጊዜ እኮ ህሊናህን ታጣህ፡፡ እንዴት ብለህ ነው አዉሬዎቹን የምታባርራቸው” ብለው ጠየቁት ዲጎገንስ ሲመልስም “ ህሊናዬየን ካጣሁ ስለመሞቴ ለምን እጨነቃለሁ” ሲል መልሷል፡፡ አስገራሚውና አዝናኝ የሚመስለው የዲዮገንስ ፍልስፍና እያዝናናም እያበሳጨም የማስተማር ሀይል ነበረው፡፡

Posted by EthioSophi Admin

Comments

  1. በጣም አሪፍ አርቲክል ነው። በዚው ቀጥሉበት ከፍልስፍናው አለም ጋር መተዋወቅ ለሚፈልጉ ሰዎች የምትሆን ሸጋ ብሎግ ናት

    ReplyDelete
  2. best men ዲዮጋን ተመችቶኛል ቀጥሉበተ ሸጋ ነው

    ReplyDelete
  3. ዉሸቶች በጣም ከመደጋገማቸዉ የተነሳ እዉነት መስሎ እየመራ ያለዉ ዉሸት ለመሆኑ ከዚ በለይ ማስረጃ የለም ስንት ትንሽ ሰርተዉ ብዙ የተነገረላቸዉ ፈላስፎች በጣም ከሚገባቸዉ በላይ አለም ያገነናቸዉ አለ ግን የዜ ፈላስፋ ህይወት እዉነትን በማስተማር ብቻ ሳይበቃዉ እራሱ በመኖር ጭምር ያስተማረ እዉነተኛ እዉነትን አፍቃሪ ሆኖ ያለፈ ግን አለም የሚገባዉን ያህል ያለወቀዉ እና ያለዘከረለት ከኔም ጭምር አባዛኛዎቻችን የዉሸቱ አኗኗሯችን ባህላችን እና ማንነታችን ስለሚቋወም ከሚገለፅልን እዉነት ይበልጥ የለመድነዉ ዉሸት ይሸለናል ስላልን ነዉ

    ReplyDelete

Post a Comment

Popular posts from this blog

የፍቅር ፍልስፍና: ፍቅር ምንድነው?

የማካቬሌ ፍልስፍና

የፍቅር ትርጉሙ