ትችት እንደ ስድብ

ለኔ ስድብ ሆኖ የሚሰማኝ ሌላው ስድብ ብሎ የሚጠላው ቃል አይደለም ።ለምሳሌ ውሻ  ለኔ የስሜት ውክልና ነው። ቃሉን የምወስደው እኔ ለቃሉ በምወክለው ስሜት ደረጃ ነው። ስለዚህ በስድብ ስሜት ካልወከልኩት ውሻ መባል ለኔ ስድብ አይደለም። ስድብ ለኔ ሌላ ምንም አይደለም።ስድብ

ለኔ ከአስተሳሰብ ደረጃዬ በታች የሆነ አሳብ እንድሰማ ማድረግ ነው። የማይመጥነኝን ማንበብ ለኔ ስድብ ነው። መስማት የማልፈልገውን አሳብ መስማት ጭቅጭቅ ነው።

ፍቅር ያሸንፋል፣ ተዋደዱ፣ ተፋቀሩ፣ በፍቅር ተነፋረቁ የሚሉት የህዝባችን የሞራል እሴቶች የሀይማኖት ሰነድ ማዳበሪያ ከመሆን ባለፈ በተግባር መገለጥ አለመቻላቸው አሳሳቢ ነው። ፍቅር የሚለው የሚሰራው ወይ በብሔር፣ወይ በሀይማኖት አንድ ሲሆኑ ብቻ ነው። በልዩነተ መገኘት የሚያመጣው ጥላቻን ነው። በመሰረቱ ፍቅር ያስፈለገው ተመሳሳይ የሆነ ሰው ባለመኖሩ የልዩነት ማጣበቂያ በማስፈለጉ ነው። ተመሳሳይ ከሆነማ አንድ ነው። ፍቅር ሰብከው እንደ ዜጋ አስተምረውን ፍቅር ፣ሰላም ምናምን ተብሎ ሲያበቃ ልዩነት ሲፈጠር የሚፈታው በአመፅ ነው። አንዱ ሌላውን ይከሳል። ሌላው አንዱን ይከሳል። አመፅ ለአንዱ ቢዝነስ ነው። ለሌላው የሰላም ዋስትና ነው። ጠንካራ ልዩነት ሲፈጠር የመጀመሪያው እርምጃ  የሰላም አማራጩን መዝጋት ነው። ፍቅር ከተግባር ካልጀመረ የስሜቱ ህልውና የቱ ጋር ነው??

መጀመሪያም በልዩነት ፍቅር ባለመኖሩ አንዱ ከሌላው ጋር አይተማመንም። ፍቅር ካለ እምነት አለ። እምነት ካለ ሰላም አለ። በፍቅር ልዩነት በእምነት ሀይል ያልተገነባ ህዝብ በልዩነቱ መሀል የሚያስቀድመው የሰላምን አማራጭ መዝጋት ነው። ከዛ ደካማው ይሞታል። አቅም ያለው ይገድላል። ድርጊቱ ጥላቻን፣ ጥላቻው ሌላ ድርጊት እየወለደ መንጎድ ነው። ነገ ገድልከኝ፣ ገደልኩህ ተብሎ መጀመሪያ የሞቱለትና የገደሉበት ችግር ሳይፈታ እንደገና ሌላ ችግር ይወለዳል። ችግር በችግር ላይ እየረራባ ይሄዳል።

አንዳንዴ "በአስተሳሰብ የተለየሁት ሌላው ተሳስቶ ነው ወይስ እኔ ተሳስቼ ?" ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ። በእርግጥ የራሴን ከኖርኩ ለራሴ ትክክል ነው። ለራሴ ስኖር ግን የምኖረው ከሌላ ሰው ጋር ነው። ስለዚህ እኔ ለራሴ ብቻ ትክክል መሆን ስለማልችል የሌላውን ስህተት እቀበላለሁ።

እዚች ፌስቡክ ላይ ከማየው ጉድ ጫና የተነሳ  በቅርቡ ፌስቡኬን እዘጋለሁ። ከመዝጋቴ በፊት ግን አጀንዳ መክፈት እፈልጋለሁ። ቆይ ግን እናንተ ኢትዮጵያውያን በብሔሩም፣ በሀይማኖቱም፣ በንግዱም፣ በምናምኑም ትክክል ነን ብላችሁ ታስባላችሁ? አወቀ ፣ ፌደል ቆጠረ የምትለው ሙሁር የሚጋልበው በእውቀቱ ልጓም ሳይሆን በስሜት ፈረሱ ነው። ሙሁር ለመሆን የግድ የብዙሀኑ ፍላጎትን ለብሶ የተማረውን መሸፈን አለበት። እዚህ ፌስቡክ ላይ የማንንም ፅሁፍ አላነብም። ላንብብ ብልስ ማን የፃፈውን አነባለሁ? ሰዎች ለምን የሌሎች ፀሀፊዎችን ፅሀፍ አታነብም ብለው ሲጨቀጭቁኝ እሺ ብዬ ታግዬ ለማንበብ ሞከርኩ ።ሁሉም ፅሁፍ ግን በአንድ ማእቀፍ ውስጥ የሚሽከረከር ነው። " ወያኔ ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣  ግንቦት 7፣ እስልምና ክርስትና" እውነት ነው የምላችሁ ጭንቅላቴ ሊፈነዳ የቀረው ደማሚት መሆን ብቻ ነው።

አንዱ ሌላውን የሚተቸው ወጥ ከሆነ መርህ ተነስቶ ሳይሆን የሌላው ስህተት ተጠቅሞ ነው። ሰው ራሱ ተሳስቶ የሌላውን ስህተት ለማረም እንዴት ይዳፈራል። እውነት ለመናገር እኔ ብሔርም ሆነ ሀይማኖት የለኝም። ወደፊትም እንዲኖረኝ አልፈልግም። የኢትዮጵያዊነት ስሜትም የለኝም። ብሳሳትም ነፃ ሆኜ የየዋህ ስህተት ነው። የሆነ ነገር ተደግፎ መሳሳት ግን የቅንነት ችግር ነው። እውነት በነፃነት እንጂ በውግንና እውቀት አትወከልም። ሌላው ቢቀር ብዙሀኑ ከሚንንጋጋልህ ሀይል ይልቅ ጥቂት በሳሎች የሚታዘቡህ ትዝብት የተሻለ አቅም እንዳለው ተረዳ። ስትፅፍ፣ ወይም የሆነ አስተሳሰብ ስታራምድ የወረደ ከሆነ ስድብ ነው።ስድቡ ለአንተ ለራስህ ትዝብት መሆኑ ነው። አንድ ነገር ልጠይቃችሁ!  ይሄ ነገር እኔ ተሳስቼ ነው ወይስ ብዙሀኑ ተሳስቶ ነው?

Posted by EthioSophi Admin

Comments

Popular posts from this blog

የፍቅር ፍልስፍና: ፍቅር ምንድነው?

የማካቬሌ ፍልስፍና

የፍቅር ትርጉሙ