የፕሌቶ ፍልስፍና

ፕሌቶን ከቀደምት የግሪክ ፈላስፋዎች ለየት የሚያደርገው በፊት የነበሩት የግርክ ፍልስፍናዎች በተወሰነ መልኩ በአንድ ጉዳይ ላይ ብቻ የሚያጠነጥኑ ሲሆኑ ፕሌቶ ግን  በሁሉም የእውቀት ዘርፎች ላይ ሰፋ ያለ ትንታኔ መስጠት መቻሉ ነበር ፡፡ደህና ደረጃ ከነበራቸው ቤተሰቦቹ ከክርስቶስ ልደት በፊት 427 ም.አ  በአቴንስ የተወለደው ፕሌቶ በምዕራባዉያን ፍልስፍና ታሪክ እጅግ በጣም ጎላ ያለ ቦታ የሚሰጠውና ከሶቅራጥስ ተማሪዎች አንዱ በመሆን ጎልቶ መውጣት የቻለ  ፈላስፋ ነው፡፡


ፕሌቶ በኖረበት ዘመን አቴናዉያን ዴሞክራሲ እየተዳከመ የመጣበት ዘመን በመሆኑና እንደ መሲህ የሚያው የቀለም አባቱ ሰቆራጥስ  በአቴናዉያን ፊት ለፊቱ በመርዝ ሲደፋ በማየቱ ለአቴናውያን የነበረው አስተሳሰብ በአሉታዊ ገጽታ የሚቀምጥ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ፕሌቶ እየዘመመ የመጣውን የአቴናዉያን ዴሞክራሲን እንዲንሰራራ ለማድረግ የተለያዩ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን ለመቀመር መነሳሳት ጀመረ፡፡ በ387 ም.አ ገደማ በአዉሮፓ ከቀደምት ጥንታዊ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንዱ ሊባል የሚችለውንና ለብዙ ተማሪዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ትምህርት የሚሰጥበትን አካዳሚ መስርቶ በመምህርነት እና ፍልስፍ በመፃፍ ከ40 አመት በኋላ ያለውን እድሜውን አሳልፏል፡፡ የፕሌቶ ስራዎች በርካታ ሲሆኑ አብዛኞቹ አስተማሪው ነበረው ሶቅራጥስ ትምህርቶችን የያዙ ነበሩ፡፡ የፕሌቶን የግል ሕይወት በየትኛውም የመረጃ ምንጭ በቀላሉ ማግኘት ስለሚቻል ወሬ ለማሳጠር ያህል ወደፍለስፍናው መግባት አስፈላጊ ነው፡፡

ሀ. የዋሻው ምሰሌ
ሰለእውቀት እድገት በሚመለከት በጣም ታዋቂ የሆነችለት ፍልስፍናው የፕሌቶ የዋሻ ምሳሌው ናት፡፡ በዚህ ምሳሌ መሰረት  ለረጅም ጊዚያት ሰዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ በዋሻ ውስጥ በጨለማ እንዳይንቀሳቀሱ ተደርገው የታሰሩ አድርጎ የተሳሉ ሰዎችን ያቀርባል፡፡ እነዚህ ሰዎች ወደ ኋላም ወደ ጎንም መንቀሳቀስ እንዳይችሉ ተደርገው በመታሰራቸው የሚመለከቱት  ከፊት ለፊታቸው ያለውን  እውነታ ብቻ ነው፡፡ ከነዚህ ሰዎች በተለየ የመንቀሳቀስ ነፃነት ያላቸው ሌሎች ሰዎች ደግሞ የተለያዩ ስራዎችን የሚሰሩ ሰዎች በዛው በዋሻው ውስጥ  ይገኛሉ፡፡ከሁለቱ መካከል ለዋሻው ብርሀን የሚሰጥ እሳት ይነዳል፡፡  የታሰሩት የሚንቀሳቀሱትን ሰዎች በግድግዳ ላይ የተሳለውን ጥላ  ብቻ ነው የሚያዩት፡፡ ነግር ግን ትክክለኛ ሰዎቹን  ማየት አይችሉም፡፡ በዋሻው ውስጥ ታስረው እንዳይንቀሳቀሱ ሆነው የተቀመጡት ሰዎች ማየት የሚችሉት የፊት ለፊታቸውን ብቻ በመሆኑ ማየት የቻሉት በዋሻው ግድግዳ ላይ የሚያንፀባርቀውን የሰዎች ጥላ ብቻ ነው፡፡ እነዚህ የዋሻ እሰረኞች የሚንቀሳቀሱትን ሰዎች ድምፅ በሚሰሙበት ጊዜ ፊት ለፊታቸው ያለውን የሰዎች ጥላ ብቻ ስለሚያዉቁ ድምፁ ከጥላው የሚመነጭ ይመስላቸዋል፡፡ ስለዚህ ለእነዚህ ሰዎች እውነት ማለት ከግድግዳው ላይ የተሳለው የሰዎች ጥላ እንጂ ትክክለኛ ሰዎቹ አይደለም፡፡ ፕሌቶ እነዚህ ታሰሩ ሰዎች የመንቀሳቀስ ነፃነት ቢኖራቸው ኖሮ በእውቀታቸው ላይ የሚፈጠረው ልዩነት ምን ሊሆን ይችል ነበር በማለት ይጠይቃል፡፡ እነዚህ የዋሻ እሰረኞች የመንቀሳቀስ እድል ቢኖራቸው እሳቱንና ሰዎቹን ስለሚያዩ የሰዎቹ ድምፅ የሚመነጨው ከጥላው ሳይሆን ከሰዎቹ እነደሆነ ይረዱ ነበር፡፡  በዚህም ከሚያዩት ጥላ በስተጀርባ ትክክለኛ እውነታ እንዳለ መገንዘብ ይችሉ ነበር - ይላል ፕሌቶ ፡፡ ሰዎቹ ከዋሻው መውጣት ቢችሉ ኖሮ ደግሞ ዋሻው ውስጥ ከነበራቸው ግንዛቤ በይበልጥ የጸሀይ ብርሀን የመሳሰሉ ሌሎች እውነታዎችን እንዳሉ ማወቅ ይችሉ ነበር፡፡

image

የዚህ ምሳሌ አሳብ አንድ ማህበረሰብ በትምህርት በሚገኝ እውቀት ብርሀን በመጠቀም ራሱን ነፃ ካላወጣ በዋሻ ውስጥ ታስረው እንደኖሩት ሰዎች የጨለማ እውቀት ነው የሚኖረው፡፡ ትምህርት ያላየኸውን እውነታ የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን የእይታ አድማስን የሚያሰፋ ብርሀን እንደሆነ ፕላቶ ያስረዳል፡፡ በዋሻው ውስጥ የታሰሩት ሰዎች መንቀሳቀስ ቢችሉ ኖሮ ከጨለማው ይልቅ ብርሀን የማየት እድል ነበራቸው፡፡ በተመሳሳይ ሰዎችም እውነትን ለመረዳት በጨለማ ውስጥ ከቆዩበት ዋሻ መውጣት ያስፈልጋል - እንደ ፕሌቶ እምነት፡፡

ለ. የእውቀት አይነቶች
ፕሌቶ ሰውን ልጅ የእውቀት ደረጃዎች  ሀ) ምስል መፍጠር ለ) እምነት ሐ) ማሳብ መ)ትክክለኛ እውቀት በሚል በአራት ዋና ዋና የእውቀት አይነቶች  በመክፈል ያስቀምጣቸዋል፡፡ ምስል መፍጠር መጨረሻው የወረደ የእውቀት ደረጃ ሲሆን ስለ አንድ ነገር ከነገሩ ጋር የሚመሳሰል ምስል መፍጠር ይሆናል፡፡ በተጨባጭ ካለው እውነታ ውጩ ሰዎች የሚመስላቸውን ነገር በመሳል የምስል እውቀት ሊፈጥሩ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በዋሻው ውስጥ ታስረው የነበሩት ሰዎች ትክክለኛ ሰዎቹን ማየት ባለመቻለቸው ድምፁ ከሰዎቹ ጥላ የሚመጣ አድርገው ከሳሉት እውቀት ጋር ሊመሳሰል ይችላል፡፡ በሁለተኛው የእውቀት አይነት ምስል በተፈጠረበት ነገር ላይ እምነት መፍጠር ሊሆን ይችላል፡፡ በተደጋጋሚ የታዩ ነገሮችን እውነተኛ አድርጎ መቀበል እና እርግጠኛ ስሜትን መፍጠር ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ እርግጠኛ የሆንበት ጉዳይ በትክክል እውነትን ሊያሳይ እንደማይችል ፕሌቶ ያስረዳል፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ያለው እውቀት በማሰብና በማሰላሰል የሚገኘው እውቀት ነው፡፡ ከተፈጠረው ምስልና እምነት ዉጪ ስለነገሩ መረጃዎችን ማጥናት ፣ መፈተሸና እና ተገቢ የሆነ እውቀት መያዝን ያመላክታል፡፡ በመጨረሻ ፕሌቶ ያስቀመጠው የእውቀት አይነት የነገሮችን ባህሪ በማጥናት፣ ግንኙነታቸውን በማስተዋል ፣ በተለምዶ ከምናየው የገሀዱ አለም እውነታ ረቂቅ የሆኑ እውነታዎችን በማጥናት የሚገኝ እውቀት ነው፡፡

ሐ. እውነት(Theory of forms)
ፕሌቶ እንደሚያምነው የሰዉ ልጆች አካባቢያቸውን በማጥናት የሚገነዘቧቸው ማንኛውም ነገሮች የእውነት ግልባጭ እንጂ ትክክለኛውን   አይደሉም፡፡ እውነት (form) ብሎ የሚጠራት ትክክለኛዋ እውነት በሆነ ቦታ ያለች፣ የማትቀያየርና ዘላለማዊ ስትሆን እኛ በምድር ላይ የምናየው ማንኛውም ነገር የዚች እውነት (form) ግልባጭ እንጂ ትክክለኛ እውነት አይደለም፡፡ ይህ ንድፈ አሳብ አይዲያሊዝም፣ የክርስትና የእስልምና ዶክትሪኖች መሰረት የሆነ ረቂቅና ሰፊ ፍልስፍና የያዘ ነው፡፡  እንደ ፕሌቶ እምነት እውነት (form) ማለት በሆነ ቦታ የሚገኝ የማንኛውም  ነገሮች ሁሉ ባህሪያት ምንጭ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ቤቲ ቆንጆ ልጅ ብትሆን ቤቲና የዉበቷ የሷ ትክክለኛ ባህሪ ሳይሆን ከእውነት (forms)  የተቀዳ ባህሪ ነው፡፡ የቤቲና ዉበቷ ትክክለኛ ማንነት በሌላ አለም ( ምናልባት በሰማየ ሰማያት) የሚገኝ ነው፡፡ እኛ እያየነው ያለው እውነት (forms)  በቤቲ ላይ ሲንጸባረቅ  ያለውን መስል ነው፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ነገር የራሱ ምንጭ የሆነ በሌላ አለም ላይ የሚገኝ ፍጹማዊ እውነት (form) ግልባጭ ነው እንደ ፕላቶ እምነት፡፡

ሰዎች በሚሞቱበት ወቅት ነፍሳቸው ወደ ትክክለኛዋ እውነት (form) ትሄድና ዉህደት ትፈጥራለች፡፡ እነዚህ እውነታዎች   (forms) አለም ከመፈጠሯ በፊት የነበሩ የማይሞቱና እግዚአብሔር አለማትንና በዉስጣቸው የያዙን ነገሮች ሲፈጥር እንደ ግብአትነት የተጠቀመባቸው ናቸው፡፡ እውነታዎቹ (forms) ምድር ላይ ላሉ ነገሮች ምንጭ የሆኑ ፣ አንዳንድ ጊዜ በምድር ላይ ራሳቸውን የሚገልጡ ፍፁማዊና ዘላለማዊ እውነታዎች ናቸው፡፡

መ) የፖለቲካ ፍልስፍና
ፕሌቶ ሰውን የአካል ክፍል እንደ አገር በመወከል በሚያብራራበት ምሳሌው ላይ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የሚኖር የዜጎች ክፍፍልን ያስረዳል፡፡ በዚህ መሰረት የአንድ ሰው ጭንቅላት የመሪን ቦታ ይወክላል፡፡ በዚህ ውስጥ ፖለቲከኞች እና የአገር መሪዎች ይገኛሉ፡፡ የሰውየው ደረት ወታደሮችን ፣ ፖሊሶችን ሲወክል የሰውየው እጅ ደግሞ ሰራተኛውን ክፍል ወዛደር ፣ ገበሬ የመሳሰሉትን ይወክላል፡፡ አንድን ማህበረሰብ መምራት የሚገባቸው በቂ እውቀትና ጥበብ ያላቸው ፈላስፋዎች እንደሆኑ (The Philosopher-king) በማስረዳት ሁሉም ዜጎች በማህበረሰባቸውን የሚሰጣቸው ሚና ብቃትንና ከተልዕኮው ጋር የሚዛመድ ባህሪን ግንዛቤ ውስጥ አድርጎ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡

የመንግስት አወቃቀርን በሚመለከት በመጀመሪያ ደረጃ በቂ እውቀት እና ብቃት ያለው ፈላስፋ ንጉስ የሚመራው አሪስቶክራሲያዊ አስተዳደር ተገቢ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ይሁን እንጂ  በፈላስፋ ንጉስ የሚመራው አሪስቶክራሲያዊ ስርአት እየተዳከመ በሚሄድብት ጊዜ በስርአቱ ውስጥ ተሸሎክልከው በሆነ መንግድ ጎልተው የወጡና ዝናና ክብር በመጠቀም ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ  ግለሰቦች አይን መሳቡ አይቀርም፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ከአገራዊ ጥቅም ይልቅ የራሳቸውን ግላዊ ፍላጎት መሰረት አድርገው ስለሚንቀሳቀሱ ስርአቱን ወደ ለየለት የንግድ ተቋም ሊቀይሩት ይችላሉ፡፡  በዚህም ገንዘብ ያላቸው ሀብታም ሰዎች ለማገዝ በሚል ፖለቲካዉን እንዲቀላቀሉ በር በመክፈት በሀብታቸው ተቆጣጥረው ስልጣንን በገንዘብ ማሽከርከር  ሲጀምሩ ስርአቱ ቲሞክራሲ ወደሚባል የሀብታሞች ስርአት ይቀየራል፡፡ ስርአቱ ሀበታሞችና የባለጸጎች መተራመሻ እየሆነ ሲሄድ የብዙሀኑ መብት እየተጨፈለቀ ይሄዳል፡፡ መብቱና ተጠቃሚነቱ እየተረገጠበት ያለው ብዙሀኑ ሲመረው ግልብጥ ብሎ በመውጣት  በሚያደርገው ትግል የብዙሀኑን ፍላጎት ያገናዘበ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ይፈጠራል፡፡ ፕሌቶ ትክክለኛ የመንግስት ስርአት በሚል በቂ እውቀት እና ብቃት ያለው ፈላስፋ ንጉስ የሚመራው አሪስቶክራሲያዊ አስተዳደርን የመረጠ ሲሆን ዴሞክራሲ የመንጋ ፍላጎት የሚስተናገድበት ስርአት የሌለው፣ በማህበረሰባዊ ክፍፍል የማይመራ አስተዳደር ከዚህ በከፋ ደግሞ ብቃት ያላቸውን የፈላስፋ መሪዎች ሚና የሚያገል  በመሆኑ ዴሞክራሲን እንደ ትክክለኛ የመንግስት አስተዳደር አይቀበልም፡፡

Posted by EthioSophi Admin

Comments

Post a Comment

Popular posts from this blog

የፍቅር ፍልስፍና: ፍቅር ምንድነው?

የማካቬሌ ፍልስፍና

የፍቅር ትርጉሙ