ስለፍቅር

ከሁሉም በፊት ለፍቅር ቅድሚያ መስጠት ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው። ሌላውን የማፍቀርና ያለማፍቀር መብት የሚወሰነው ራስን ከማፍቀር ግዴታ ነው።


ፍቅር ምንድነው? መልስ የለውም። ለምን?  ፍቅርን ለየት የሚያደርገው በአንድ ጉዳይ ላይ የሚሰጡ ተፃራሪ እልፍ መልሶች ትክክል የሚሆኑበት በመሆኑ ነው። ፍቅር እውነትም ወይም ውሸትም አይደለም።  ስለዚህ የፍቅር ትርጉም ምላሽ ቢሳሳትም ትክክል ፣  ትክክል ቢሆንም የተሳሳተ ነው። ከምንም በላይ ወሳኙ ግን ራሱ ፍቅር ብቻ ነው።
image

ማንኛውም ሰው ፍቅር የሚይዘው  በህይወቱ አንድ ጊዜ ብቻ ነው። እሱም ራሱን ያፈቀረበት ነው። ሌላው ፍቅር የሚነሳው ከዚህ ለራስ ከሚኖር ፍቅር ነው።

ፍቅር አንድ ነው። አይለወጥም። አይከፋፈልም። ፍቅር አይለያይም። ለአባትህ የምትሰጠው ፍቅር ለእናትህ የምትሰጠውን ፍቅር ነው። ለፍቅረኛሽ የሚትሰጪው ፍቅር ከወንድምሽ የነጠቅሽውን ነው። ፍቅር የተለያዬ የሚመስለን ከራሱ ፍቅር ሳይሆን ለፍቅር ከሚሰጠው ምላሽ ነው። ፍቅርማ ምንጊዜም አንድ ነው። ለሁሉም የሚሰጠው ፍቅር የሚነሳው ለራስ ከሚኖር ፍቅር ነው።

ፍቅርን መሆን ለራስ ነው። ሌለውን የምታፈቅረው ለራስህ ብለህ ነው። ለሌላ የምትሰጠው ፍቅር የሚነሳው ለራስህ ካለህ ፍቅር ነው።  ልዩነት ካለው ለሌላው የምትሰጠው ፍቅር ከራስህ የሚቀነስ መሆኑ ነው።

ፍቅር በራሱ እውር ነው። ብርሀን የሚበራለት በሰው ልብ ውስጥ ሲገባ ነው። ፍቅር በራሱ ምንም ነው። ትርጉሙን የሚያገኘው በአፍቃሪ ውስጥ ራሱን ሲገልፅ ነው። ሰው ባይኖር ኖሮ ፍቅር ብቻውን ጥላቻ ነው። ፍቅር ያለሰው ባዶ  ጥላቻ ነው። ፍቅር ሰውን የሚያፋቅረው ከጥላቻ ለመሸሽ ነው።

የሚያፈቅርሽን ሰው ሁሉ እንደጥፋተኛ አትኮንኒው። ማፍቀር መብት ነው። አንቺ ፈለግሽም አልፈለግሽ አንቺን ማፍቀር የማንኛውም ሰው ተፈጥሯዊ መብት ነው።  ውበትሽ የአንቺ ቢሆንም ያፈቀረበት ስሜቱ የራሱ ነው። ስለዚህ በአንቺ ውበት የማፍቀር መብት የሁሉም ነው። ግዴታ ሊሆን የሚችለው የአንቺ የማፍቀር መብት በመጣስ ለፍቅር ሲያስገድድሽ ብቻ ነው። ወዶ ያፈቀረ የማይፈቀረው ተገዶ ነው።

ብዙ ሰዎች በፍቅር ውስጥ የሚፈጠር ተቃርኖ ጥላቻ እነደሆነ ይሰማቸዋል። እውነታው ግን ሌላ ነው። በፍቅር ውስጥ የሚፈጠር ተቃርኖ ሁሉ ጥላቻ ሳይሆን በአብዛኛው ፍቅርን ላለማጣት የሚደረግ የፍቅር ተጋድሎ ነው።

ቅናት የሌለበት ጎጆ የሬሳ ሳጥን ነው። ፍቅር ሲታመም መፍትሄው በቅናት መፈወስ ነው። ቅናት ሳይኖር ፍቅር ከታመመ ግን መፍትሄው መለያየየት ብቻ ነው። በቅናት ሳይታከም የታመመ ፍቅር መሞቱ አይቀሬ ነው።  ተሰለቻችቶ ከመቀጠል በፍቅር መለያየት መፍትሄ ነው።

አልፎ አልፎ ቅናት የተለዬ ገፅታ አለው። ፍቅር እየጦዘ ሲሄድ መድረሻው ጥላቻ ነው። ቅናት ግማሹ ፍቅር ፣ ግማሹ ጥላቻ ነው። ወደ ጥላቻ የሚያመዝን ቅናት መነሻው ፍቅርን ማካፈል ሳይሆን ሁሉንም ወደራስ የማድረግ ራስ ወዳድነት ነው።

ብዙ ሰዎች ለአንተ ፍቅር እንደሌላቸው የሚሰማህ አንተ በራስህ ፍቅር ስሌለህ ነው። የሌሎችን ፍቅር የምትረዳው በራስህ ፍቅር ተርጉመህ ነው።

ፍቅር ብቻውን ምንም ነው። ማፍቀርህ ሙሉ የሚሆነው ያፈቀርካትን ልጅ ፍቅርህ እንዲሰማት ስታደርግ ነው። ያለዚያማ  ማፍቀርህ የራስህ ስሜት ብቻ ሊሆን ነው። ስለዚህ ፍቅርህን ማጋራት የምትችለው እሷን ማፍቀርህ እንዲሰማት ማድረግ ስትችል ነው። ይህን የምታደርገው ደግሞ የሷን የፍቅር ምርጫ ስታከበር ነው።

Posted by EthioSophi Admin

Comments

Popular posts from this blog

የፍቅር ፍልስፍና: ፍቅር ምንድነው?

የማካቬሌ ፍልስፍና

የፍቅር ትርጉሙ