ማንን ነው የምንከተለው: እውቀት ወይስ ሰው?

ቅልብጭ ባለ አማርኛ እውቀት ማለት የእውነት  የአስተሳሰብ ውክልና ማለት ነው። እውነት ደግሞ የመሆን ህልውና ውክልና ማለት ነው። በእውነት ትርጉም ላይ የሚሰጠው አሳብ አንፃራዊ ቢሆንም የእውቀትን ትርጉም ተጨባጭ በሆኑ መለኪያዎች ፈትሾ ማስቀመጥ ይቻላል። እውቀት ማለት ሰው ማለት አይደለም። እውቀት እና አዋቂ ይለያያሉ።


እውቀት ማለት የግለሰብ ንብረት ሳይሆን በጋራ ሊያውቀው የሚችል  የሁሉም ሰው መብት ነው።እውቀት ማለት ሊረጋገጥ የሚችል እውነተኛ አስተሳሰብ ማለት እንጂ የግለሰብ ሀብት ማለት አይደለም።  እውቀት ከአንድ ታዋቂ ሰው የሚጫን ሳይሆን እውነትን ማረጋገጥ የሚችል ማንኛውም አይነት አስተሳሰብ ማለት ነው። ስሜት ኮርኩሮ የስሜት መረጃ ማደራጀት እውቀት አይፈጥርም። ስሜት ሲደራጅ የሚፈጥረው እውቀት ሳይሆን እውነት የሚመስል ስሜት ነው። ማንኛውም ሰው ማረጋገጥ ስለሚችለው እውነት የመሰለውን አስተሳሰብ በማራመድ እውቀት የመፍጠር ብቃት አለው ብቻ ሳይሆን ማንም የማይነካበት የራሱ መብት አለው ። እውቀት የሚፈጠረው ግለሰብ በማምለክ ሳይሆን አንዱን እውቀት ከሌላው በማወዳደር ነው። ውድድር ደግሞ መተዛዘል ሳይሆን የአሳብ ፍጭት ነው። በውድድር የአሳብ ተቃርኖ ሂደት አንዱን እውቀት መቃወም፣ መለወጥና ማሻሻል ለአበሻ እንግዳ ሊሆን ቢችልም በእውቀት የበለፀጉት አገራት የተለመደ ነው። እኔ የራሴን አማራጭ እውቀት ለማቅረብ ራስል ወይም ዊሊያም ጀምስ ተሳስቷል ብዬ ልነሳ እችላለሁ። በተቃውሞ የሚፈጠር የአሳብ ፍጭት ግለሰብ ስለፈለገው የሚፈጠር ስላልፈለገው የሚቀር ሳይሆን እውቀትን የመፍጠር ሂደት ተፈጥሯዊ ባህሪ አስገዳጅነት የተፈጠረ በመሆኑ የአሳብ ፍጭትን መቀበል አስፈላጊ ነው። እውቀት ታዋቂ ሰው የሚያራምደውን አስተሳሰብ መደገፍ መስሎ የሚሰማን ካለን መጃጃል ውስጥ ነን። እውቀት በጋራ የአሳብ ፍጭት የሚገነባ የሁሉም ሰው መብት ከሆነ እንትናን አትንካ የሚለው እምቡር እምቡርን ምን አመጣው??

የአሳብ ፍጭትን ከግለሰብ ስሜት መነጠል ያስፈልጋል። አንድን ሰው ታከብረዋለህ ማለት አትተቸውም ማለት አይደለም። አንድን ሰው ተቸኸው ማለት ጠላኸው ማለት አይደለም። ደግፍከው ማለትም ወደድከው የሚለውን አያመላክትም። አንዱ ሌላውን ተችቶ ታዋቂ በሆነ ቁጥር እሱ የሄደበትን ትችት ሌላው ሲጠቀመው ለገላጋይ የሚያስቸግር ያዙኝ ልቀቁኝ አምባጓሮ ውስጥ መግባት ነውር ነው። ጨዋ ነኝ ከሚል ህዝብ አይጠበቅም። ጨዋነት መደገፍና ዝምታ ሳይሆን በከፍተኛ የአሳብ ፍጭት ውስጥ በብቃት የማለፍ ማንነት ነው። ፅሁፍ መፃፍን በውርስ ያገኘው የግል ሀብት እስኪመስል ድረስ ከሰው በተቃራኒ ከፃፍክ ነብርይ አየኝ በላት የጩኸት ጋጋታ ቢያንስ ፌስቡክ አጠቃቀም ከሚያውቅ ሰው አይጠበቅም። ቀድሞንስ ማን ማንን ነካና  ነው እሱን አትንካ የሚባለው? የፀሀፊን ስልጣን ማን ለማ ሰጥቶ ነው አንዱ ሌላውን የሚጠብቀው? ግልፅ ያልሆነው ነገር እውቀት ነው ወይስ ግለሰብ የምንከተለው የሚለው ጥያቄ ነው። ታወቀም አልታወቀ አስተሳሰብ የጋራ ሀብት በመሆኑ በአስተሳሰብ በሚያደርገው ተሳትፎ ሊተች ይችላል። የሚተቸው ጥቅል አስተሳሰቡ ሊሆን ይችላል። እውቀትን የሚከተል የሌላውን እውቀት የማግኘት መብት አይገድብም። ግለሰብን የሚከተል ግን የሰው ስልጣን ሲጠብቅ የሚውል የሌላ አስተሳሰብ ዘበኛ ነው።

Posted by EthioSophi Admin

Comments

Popular posts from this blog

የፍቅር ፍልስፍና: ፍቅር ምንድነው?

የማካቬሌ ፍልስፍና

የፍቅር ትርጉሙ