ውሸት አልወድም የሚል ውሸት

ውሸት አልወድም ማለት በራሱ ውሸት ነው። ሁሉም የራሱን ስሜት እውነት አድርጎ በሚረዳበት አገር እውነት የሚፈልግ ሰው የለም። ከእውነት ይልቅ የሚፈልገው ነገር ቢኖር ራሱ ከፈጠረው ውሸት ውስጥ እውነት የሚመስል ነገር ነው።



እውነት ከሰዎች ዘንድ የምትጠፋው በሁለት መልኩ ነው። አንዱ ሰው ራሱን በውሸት ሲሞላ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሰው በራሱ ስሜት ተሞልቶ ህሊናው ሲዘጋ ነው።

ሁሉም የራሱን ስሜት ወደ እውነት ሲጮህ አንተ የራስህን እውነት ወደነሱ ብትጮህ ዝምታ ነው። በስሜት ጩኸት ውስጥ ያለ የእውነት ድምፅ የሚሰማው ለተናጋሪው ብቻ ነው። ከዚህ የሚገኘው ትርፍ በራስ እውነት መሰቃየት ብቻ ነው።

ከብቸኝነት የሚጎዳው ነገር በአካልህ በመለየትህ ሳይሆን በአስተሳሰብ በመነጠልህ የሚሰማህ የህሊና ብቸኝነት ነው። በአስተሳሰብ የሚበልጥህን በእልህ ስሜት ትከተለዋለህ። በአስተሳሰብ የሚወርድብህ ሲበዛ ግን ወደ ታች ለመውረድ ትሰቃያለህ። የአስተሳሰብ አቀበት በቁጭት ስሜት ያልቃል። የአስተሳሰብ ቁልቁለት ግን በህሊና ውርደት አንገት ያስደፋል።

ከሁሉም ነገር በላይ እኔ የሚያሳዝነኝ ነገር ሰዎች እንደኔ ተመሳሳይ አስተሳሰብ አለማራመዳቸው ሳይሆን እንደኔ ማሰብ አለመፈለጋቸው ብቻ ነው።

ሁሉም መስማት የሚፈልገውን ብቻ የሚሰማ ከሆነ ከምትነግረው እውነት የተሻለ ዝምታህ እውነት ነው።

ለእውነት መኖር ቢከብድኳ ትክክል ለመሆን መኖር ቀላል  ነው። ስህተት መሆን ቀላል ቢሆንም ለእውነት ከመኖር በላይ ግን ቀላል አይሆንም።

እርስ በርሳችሁ ስትጋገሩ መደማመጥ ካልቻላችሁ ከብቶች ናችሁ። እናንተን ከከብቶች የሚለያችሁ በአራት እግር አለመሄዳችሁ።

እጅግ በጣም የሚያስጠላኝ ነገር ቢኖር ተመሳሳይ አሳብን ለረጅም ጊዜ መናገር ነው። ተመሳሳይ አሳብን ለረጅም ጊዜ መደጋገም የሚያሳየው ነገር ቢኖር አእምሮ ማሰብ አቁሞ የአንድ  አሳብ ብቻ መጋዘን መሆኑን ነው።

Posted by EthioSophi Admin

Comments

Popular posts from this blog

የፍቅር ፍልስፍና: ፍቅር ምንድነው?

የማካቬሌ ፍልስፍና

የፍቅር ትርጉሙ