የመንጋ ሙህርነት
እውነት የምትቆመው ተገታትለው በሚከተሉ የመንጋ ድጋፍ ሳይሆን በራሷ የጥንካሬ ብቃት ነው። በመንጋ አጀብ የሚመራ ሙሁር የሰካራም ስሜት የሚያዝናና የጠጅ ቤት አዝማሪ ማለት ነው። ከመንጋው ፊት መሰለፍ የሚያሳየው መሪነትን ሳይሆን ለመሻማት የሚያመች ቦታን መምረጥ ነው።
ከመንጋ ፊት መሰለፍ ፍትፍት ሲገኝ ከሌላው ቀድሞ እጅን ለመሰንዘር እንዲያመች፣ መከራ ሲመጣ ወደ መንጋው ዞሮ ለመደበቅ ብቻ ነው።
የአስተሳሰብ መሪነት ከመንጋውቀ ፊት መሰለፍ ሳይሆን ከመንጋው ራቅ ብሎ በመቆም አደጋን በራስ ጥንካሬ በመጋፈጥ ራስን ሆኖ መንጋውን እንዲሆን ማድረግ የሚያስችል ብቃት ነው። የመሪ ሚና በራስ አቋም መፅናት የሚችል ስብዕና እንጂ በመንጋው ላይ በመደገፍ የሚገኝ ጥንካሬ አይደለም። መንጋው በባህሪው የእውነትን ሳይሆን የነፋስን አቅጣጫ ተከትሎ የሚነጉድ በመሆኑ ጠንካራ መሰረት ሊሆን አይችልም። ጠንካራ ማንነት በራስ ጥንካሬ እንጂ ብዙሀኑን በማጃጃል በሚገኝ ድክመት የሚገነባ አይደለም።
የአስተሳሰብ መሪ የመሆን ብቃት ከመንጋው ፊት በመሰለፍ ከመንጋው ጋር መተሻሸት ሳይሆን በአስተሳሰብ ርቆ በመቆም መንጋውን ወደ ሚፈለገው ሳይሆን መሆን ወዳለበት መምራት ነው። ከመሰለፍ ውጪ ብቃት ከሌለ ለመሰለፍማ ከመንጋው በምን ተለዬ? ከመንጋው ፊት አብሮ መሰለፍ ቦታ መያዝ እንጂ መምራት አይደለም። ከፊት መሰለፍ አንድም ለሽሚያ እንዲያምች ወይም ከመንጋው ለመሾጎጥ እንጂ በራስ ብቃት ለውጥን ለማምጣት አይደለም። ከአሰላለፉ ባህሪ የተነሳ የብዙሀኑ ሚና እውነትን ረጋግጦ መጨፍለቅ እንጂ አጥርቶ ማንጠር አይደለም። የመሪ ሚና መንጋው እውነትን ከረገጠ በትኖ እውነትን ማሳየት፣ እውነትን ካመለጠ ጎትቶ ማምጣት እና እውነት ጋር ካልደረሰ መርቶ ማድረስ ነው። ለዚህ ሚና ደግሞ በሁሉም የብቃት ደረጃ ከመንጋው ተለይቶና ርቆ መቆም ያስፈልጋል። መንጋው ውስጥ ያለውን ለማጯጯህ የመንጋው ድምፅ በቂ ነው። የመሪ ሚና ከጩኸቱ የጠራ ድምፅ ማውጣት ነው። ጥቂት ብልጣ ብልጦች ከመንጋው ፊት ተሰልፈው የመንጋውን የለውጥ ሂደት የሚገድቡ ከሆነ የመጨረሻው አማራጭ መንጋውን ከኋላ በመንዳት ወደ ለውጥ ማስደንበር ይሆናል። ያኔ ከመንጋው ለመሻማት ከፊት የተሰለፉት የለውጥ እንቅፋቶች እጣ ፋንታ በመንጋው መጨፈለቅ ይሆናል።
Comments
Post a Comment