የማካቬሌ ፍልስፍና

እንደአለመታደል ሆኖ ከሌሎች ፈላስፋዎች በተለየ መልኩ ስሙ የተበላሸበት ሰው ነው -ማካቬሊ ፡፡ አንድ ሰው ማካቬሊያን ነህ ካለህ አላማዉን ለማሳካት የማይጠቀመው መንገድ የለም ማለቱ ነው፡፡ ማካቪሊያን መደበኛ ተቀባይነት ያለውን የስነ ምግባር ደረጃ በመጣስ ለግል ጥቅም ሲባል በማጭበርበር ወይም በሴራ በሉት አላማን የሚያሳኩበትን ሂደት የሚያሳይ ሆኖ ዛሬም ድረስ የተሳለ ጥቁር ገፅታ ነው፡፡


image

በፖለቲካ ሲሰነጠቅ ደግሞ  ስልጣን ለማግኘት አግኝቶም በስልጣን ለመቆየት መጥፎም ነገር ቢሆን ይደርጋል በሚለው ትርጉም ሊወሰድ ይችላል፡፡ ማካቬሊ ብዙ ስራዎች ቢኖሩትም እኔ ግን ያገኘሁት ልዑሉ ወይም The Prince የሚለው ስራዉን ነው፡፡ ማካቬሊ በዚህ ስራዉ ያልተለመዱ እሱንም ግብረ ገብ የጎደለው ፈላስፋ ያሰኘውን ለፖለቲካ መሪዎች ስልጣን ማራዘሚያ የሚሆኑ ምክሮች አስቀምጧል፡፡ በእርግጥ ደጋፊዎቹ ትክክለኛውን እውነታ በፖለቲካ ( Political Realism) ውስጥ ያስቀመጠ ግልፅ ሰው በሚል ይከራከሩለታል፡፡  እጥር ምጥን ያለችዉና በከተማችን በየመፅሀፍ መደብሩ እንደልብ ማግኘት የምትችሏት The Prince የተሰኘችው ስራዉ ያላዛቸው ጉድ የለም፡፡ የማካቬሊ ፍልስፍና ለመረዳት ሌሎች ስራዎቹን ማንበብ ቢጠበቅብኝም ለመንደርደሪያ ያህል The Prince በቂ ነው፡፡

በሙሉ ስሙ ኒኮል ዲ በርናንዶ ዲ ማካቬሊ በሚል ዘለግ ያለ መጠሪያ የሚታወቀው ማካቬሊ ትውልዱ በጣሊያን ፍሎሬንስ ሲሆን በዘመናዊ የፍልስፍና ታሪክ የመጀመሪያውን የፖለቲካ ፍልስፍና ያበረከተ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ ራሱን እንደ ፈላስፋ የማይቆጥረው ይህ ሰው ከፍልስፍና ባሻገር በታሪክ አዋቂነቱ፣ በስነ ፅሁፍ ብቃቱ እና ለረጅም ጊዚያት ባገለገለበት የዲፕሎማት ሙያው የሚታወቅ ሰው ነው፡፡ ማኬያቪሊ የምዕራባዉያኑን ፍልስፍና ከመካከለኛው ዘመን ድንግዝግዝ ውስጥ ፈልቅቀው ካወጡት ሙሁራን አንዱ ነው፡፡ አገሩን በዲፕሎማትና በሙሁርነት ካገለገለት የስኬት ህይወቱ ጀርባ ብርቱ የሆነ መከራና እንግልትን ተጋፍጧል፡፡ በመጨረሻም ህይወቱን ወደ ፅሁፉ አለም በማሻገር ዛሬም ድረስ አወዛጋቢ የሚባልለትን ስራ አበርክቶ አልፏል፡፡

ፍልስፍናው
እንደነገርኳችሁ የማቀርብላችሁ ፍልስፍና ልዑሉ  The Prince የሚለው መፅሀፉ ላይ ያገኘሁትን አሳብ ነው፡፡ በዚህ ስራው ማኬቬሊ ብዙዎች ስልጣንን በጥሩ ስነ ምግባር አግኝቶ ከመጠቀም አንፃር የሚያዩበትን ሂደት ገልብጦ አስቀምጧል፡፡ አንደ ማኪያቬሊ እምነት ስልጣንን ህጋዊ እና ህገወጥ በሚል ለመመዘን የሚያስችል የሞራል ደረጃ የለም፡፡ ለማኬቬሊ በኃይል የበለጠ የማዘዝ መብት አለው፡፡ ዋናው ጉዳይ በየትኛውም መንገድ ስልጣንን መያዝና ማስቀጠል ነው፡፡ ደግነትና ስልጣን አንድ ላይ አይሄዱም፡፡ የስልጣን ህጋዊነት የሚወሰነው በስልጣኑ ላይ ለመቆየት የሚያስችል ኃይል ባለቤት በመሆን እንጂ ደግ ሰው በመሆን አይለም፡፡ ማኬቬሌ አንደሚለው ጥሩ ህግና ጥሩ ወታደር ለሰላማዊ ስልጣን መኖር አስፈላጊ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ መብትን መጣስ በራሱ ህጋዊነትን ስለሚፈጥር ጥሩ ህግን በጥሩ ወታደር መተካት ግድ ይላል፡፡ ማካቬሊ እንደሚለው “ ጥሩ ህግ ያለ ጥሩ ወታደር አይመጣም” ፡፡ የጥሩ ወታደር መኖር ጥሩ ህግን ይፈጥራል፡፡ ኃይልን አስፈላጊ በሆነ ጊዜ አለመጠቀም ጥሩ ነው የሚባለውን ህግንም የሚጎዳ ነው፡፡

ማካቬሊ እንደሚለው ጠንካራ መሪ ምንጊዜም ቢሆን የቃሉ ተገዢ አይደለም፡፡ ቃልህን ለመጠበቅ ስትል አደጋ ውስጥ ራስህን ካስገባህ ለማካቬሊ ሞኝ ሰው ነህ፡፡ ሰዎች ቃልህን ትጠብቅላቸው ዘንድ እነሱ ራሳቸው በቃላቸው የማይገኙ ወላዋዮች ናቸው፡፡ በመሆኑም ብልህ መሪ “ ለሚያደርገው ድርጊት ሁሉ የተለያዬ ቀለም መስጠት አለበት፡፡ በዚህም አስፈላጊ ሲሆን መዋሸት ገፋ ሲልም ማታለል ያስፈልጋል” ፡፡ ጥሩ ነው ብለህ ያመንከው ሰው አንድ ቀን ከአንተ መጥፎነት በላይ ሊጎዳህ ይችላል፡፡ ስለዚህ አንደ ማኬቬሌ እምነት አንድ መሪ መቼና ለምን መጥፎ ባህሪን መጠቀም እንዳለበት በዙሪያው ካሉ ሰብስቦች  ይበልጥ ቀድሞ ማሰብ መቻል አለበት፡፡ ማኬያቬሊ አለም ጥሩና መልካም ስነ ምግባር ብትመራ ደስ ይለው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በተጨባጭ ከሚታየው እውነታ አንፃር ጥሩ ሆኖ መገኘት ያስበላል ብቻ ሳይሆን ያስገሸልጣል፡፡

አስደንጋጭ ከሆኑት የማኬቬሊ አሳቦች አንዱ በወረራ የተያዘን የባዕድ መሬት እንዴት ማስተዳደር እንደሚቻል ያቀረበው አሳብ ነው፡፡ ማኬቬሌ በወረራ የተያዘን የሌላ ህዝብ ግዛት ለማስተዳደር ሁሉንም ድምጥማጡን አጥፍቶ በራስ ሰው መተካት ወይም ደግሞ በሁሉም ግዛቶች ኃይለኛ የሆነ ታማኝ የራስን ሰው ሾሞ መምራት ይገባል፡፡

የፖለቲካ ድጋፍን በሚመለከት ማካቬሌ "ህዝብህን ውደደው እንጂ አትመነው " የሚሏት አይነት ሙድ አስፈለጊ ናት ይላል፡፡ እንደ ማኬቬሌ እምነት የመሪ የስነ ምግባር መመዘኛ እና ብዙሀኑ የሚለካበት የስነ ምግባር መመዘኛ የተለያዩ ናቸው፡፡ እዚህ ላይ ማካቬሌ ብዙሀኑ ይከተለው የነበረውን የክርስትና የሞራል ስነ ስርአት በብርቱ መተቸት ይጀምራል፡፡ እንደ ማኬቬሊ እምነት የክርስትና የስነ ምግባር አስተምህሮ   “ ብዙ ሞኞችን ፈጥሮ በመጥፎ ሰዎች አደን ኢላማ ውስጥ እንዲገቡ  ያመቻቸ አስተሳሰብ ነው ” ስለዚህ ብዙሀኑ ለስላሳ የሞራል ህጎችን ተከትለው መኖራቸው ለስርአትህ ሰላምና መረጋጋት የጎላ አስተዋፅኦ አለው፡፡ ሀይማኖት ለማካቬሌ እውነተን የሚያንፀባርቅ ሳይሆን ብዙሀኑ መካከል ዉህደት ፈጥሮ የተርጋጋ ስልጣን እንድታገኝ የሚረዳህ መሳሪያ ነው፡፡  መሪዎች ግን ብዙሀኑ በሚመሩበት የሞራል ህግ መመራት የለባቸውም፡፡ የመሪዎቹ ውሳኔ ሁልጊዜ ከሁኔታዎች ጋር ራሱን የሚቀያይር መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም የብዙሀኑ አስተሳሰብና ፍላጎት ምንጊዜም ቢሆን በጠበቅከው የሚገኝ ሳይሆን በየጊዜው የሚለዋወጥ ነው፡፡  ማኬቬሊ ያለውን ቃል በቃል ስተረጉመው  “ ብዙሀኑ በልቶ በቃኝ የማያውቅ፣ እስስት፣ ዉሸታም ፣ ወላዋይ መንጋ ነው፡፡ አንተ ስታሸንፍ ከአንተ ጎን ይሰለፋል፡፡ አንተ ደክመህ እርዳታ ስትፈልግ ደግሞ በአንተ ላይ ይመጣብሀል ”  በመሆኑም ጥሩ መሆን ያለብህ ብዙሀኑ ስለሚከተለው ሳይሆን ለአንተ የሚጠቅም ከሆነ ብቻ ነው፡፡ የማካቬሌን ፍልስፍና መጥፎ ሆኖ ቢታይህም ከእውነት የራቀ ነው ብሎ መውሰድ ግን አይቻልም፡፡ በመሆኑም ገልብጠህም ተማበርበት በቀጥታ ማኬቬሌ ካለው አሳብ የተማረው የመጀመሪያው ሰው ልትሆን ግን አትችልም፡፡ ከአንተ በፊት ጠልተውት የተማሩበት በርካቶች ናቸውና፡፡

Posted by EthioSophi Admin

Comments


  1. ማካቬሊ የበለጠ አብይ በእጥፍ ክፋት ለሳቡን ይዞል

    ReplyDelete
  2. እኔ በጣም ነው ሃሳቡ የሚመቸኝ

    ReplyDelete

Post a Comment

Popular posts from this blog

የፍቅር ፍልስፍና: ፍቅር ምንድነው?

የፍቅር ትርጉሙ