የኢትዮጵያ ታሪክ: እንደሆነው ወይስ እንደሚመስለው?

 

በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያለኝ አመለካከት በጥርጣሬ የታጀበ (sceptical) ሊባል የሚችል ነው። ሌላውን ኢትዮጵያዊ አሳመነም አላሳመነ ለዚህ አመለካከት መፈጠር ምክንያት የሆኑኝን አሳቦች ማስቀመጥ እችላለሁ።

በመጀመሪያ አሁን የምናውቀው የኢትዮጵያ ታሪክ ባብዛኛው የተዋቀረው ከቀጥተኛ ምንጮች (primary Sources) መረጃ ይልቅ በተዘዋዋሪ የመረጃ ምንጮች ( Secondary Source) እንደሆነ ይሰማኛል። በታሪካዊ ፅሁፍ ግንባታ ከታሪክ ሂደቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው የመረጃ ምንጭ መጠቀም ከምንም በላይ የታሪኩን ተአማኒነት የተሻለ የሚያደርገው በመሆኑ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የአመኔታ ጥንካሬ የሚፈጥር የመረጃ አጠቃቀም እንደነበረ አድርጌ ለመቀበል እቸገራለሁ። በታሪክ ፀሀፊዎቻችን ቀጥተኛ የታሪክ መረጃ ምንጭ ተደርጎ የሚወሰድ ቢኖርኳ በወቅቱ የፖለቲካ ሀይል የነበራቸው አካላት ተፅእኖ ስር የነበረ በመሆኑ እንደ ቀጥተኛ ምንጭ ተደርጎ የሚወሰድ አለመሆኑ ነው።በሌሎች ማህበረሰቦች ውስጥ እንደሚታየው ከማንኛውም ተፅእኖ ነፃ የሆነ ገለልተኛ የታሪክ ፀሀፊ የለም። ለምሳሌ ሔሮድተስ በመባል የሚታወቀው ጥንት ግሪክ የታሪክ ፀሀፊ ታሪክን የፃፈው ከእለታዊ አዋውሉ እስከ አጠቃላይ ሙያዊ ህይወቱ ድረስ በወቅቱ ከነበሩት ሀይሎች ተፅእኖ ነፃ በመሆን በታሪክ ሂደቱ እውነታ ላይ በመመስረት ነበር። እስከማውቀው ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ ራሱን ችሎ ገለልተኛ በሆነ መንገድ ታሪክን የፃፈ ግለሰብ ወይም ተቋም ነበረ ማለት አይቻልም። በኢትዮጵያ የታሪክ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ ታሪክ ፀሀፊዎች ከነገስታቱ እና ከወቅቱ ሹማምንት ጋር ጥብቅ ቁርኝነት የነበራቸው በመሆኑ ታሪክን የፃፉት ከተቆራኙበት አካል ፍላጎት አንፃር እንጂ ከታሪክ ጥናት አንፃር ነበር የሚል እምነት የለኝም። በዚህ የተነሳ እነዚህ የሹማምንት አጎብዳጆች የፃፉትን ተረት እንጂ ታሪክ እንደሆነ ለመቀበል ያስቸግራል። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የታሪክ ጥናት በራሱ ያልተለመደ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ታሪክ ፀሀፊዎች ራሳቸው በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የውጪ አገር የታሪክ ፀሀፊዎችን እንደ መረጃ በስፋት ሲጠቀሙ ታዝቢያለሁ። ስለዚህ ይህ የሚያሳየው አሁን የምናውቀው የኢትዮጵያ ታሪክ የታማኝነት ችግር ውስጥ ያለፈ በመሆኑ ትክክለኛ ታሪክ እንደሆነ ለመቀበል ያስቸግራል።

በሌላ መልኩ የኢትዮጵያ ታሪክ እስከነ ታማኝነት ችግሩም ቢሆን የተከተለው መንገድ ክስተቶችን፣ የግለሰብ ስሞችን፣ የጦር አውድማዎችንና የመሳሰሉትን ታሪካዊ ሂደቶች የመገልበጥ ሂደት ላይ በእጅጉ ጥገኛ የሆነ በመሆኑ ነው። ከዚህ በተቃራኒ ትክክለኛ ታሪክ ሊፃፍ የሚገባው ከእያንዳንዱ ታሪካዊ ክስተት በመነሳት መረጃ የማጥናት፣ የመተንተንና የታሪክ ሂደቱን በፅንሰ አሳብ የማስቀመጥ ሂደትን በተከተለ መንገድ ነው። በአንፃሩ የኢትዮጵያ ታሪክ ከባልዲ ውሀ የመቅዳት ያህል ክስተቶችን በቀጥታ የመገልበጥ ሂደት ነው የሚል ግላዊ እምነት አለኝ። በመሆኑም ሀ) ታማኝነት ያላቸውን የታሪክ የመረጃ ምንጮች የማስተናገድ ችግር የከፋ በሆነበት ለ) ጥናታዊ የሆነ የታሪክ ትንታኔ መንገድን የመከተል ችግር ያለበትን የኢትዮጵያ ታሪክ ተረት የሚመስል ታሪክ እንጂ ትክክለኛ የሆነ ታሪክ አድርጌ ለመቀበል እቸገራለሁ።

Comments

Popular posts from this blog

የፍቅር ፍልስፍና: ፍቅር ምንድነው?

የማካቬሌ ፍልስፍና

የፍቅር ትርጉሙ