ኢማኑኤል ካንት

ኢማኑኤል ካንት በምዕራባውያን ፍልስፍና ታሪክ የሚሰጠው ድርሻ እጅግ በጣም የጎላ ነው፡፡ የካንት የ80 አመታ ህይወት እጅግ በጣም ጭምት በሆነ ሂደት የተሞላ ነው፡፡ ካንት በዘመኑ ከተወለደባት ፑርሺያ ውጭ እንደሌሎቹ ፈላስፋዎች ከቦታ ወደ ቦታ የመዘዋወር  ልማድ አለመኖር ብቻ ሳይሆን በፖለቲካዊና ማህበራዊ ተሳትፎውም ደካማ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ በነዚህ ሂደቶች ውስጥ ተሳትፎ የጎላ ታሪክ ባይመዘገብለትም በመመህርነትና በፍልስፍና ፀሀፊነት ያሳላፋቸው ጊዚያቶች ከሌሎች ፈላስፋዎች በተለየ መልኩ ከጥበብ አናት ላይ ሊያስቀምጡት በመቻላቸው ካንት ህይወቱን በሙሉ የሰጣት ፍልስፍና አላሳፈረችውም፡፡

በጣም ሐይማኖተኛ ከሆኑት ጀርመናዊ ቤተሰቦቹ በ1724 አ.ም.  በፐርሺያ ጀርመን የተወለደው ካንት በሕይወቱ እጅግ በጣም ጥንቁቅና ለሚያምንበትን ጉዳይ ራሱን የሚሰጥ ሰው እንደነበር ይነገራል፡፡ የሀይማኖተኛ ቤሰቦቹ ተፅዕኖ በግል ህይወቱም በፍልስፍናውም ጠንካራ ተፅዕኖ ፈጥረውበት የነበረው ካንት የልጅነት ሕይወቱ የሚታወቀው በጭምትነቱ ቢሆንም የአካባቢው ሰዎች ማለዳ ላይ ልጅ ካንት በሰፈራቸው ሲያልፍ ሰአታቸውን ያስተካክሉ እንደነበር እና ለአካባቢው ሰዎች የታታሪ ምሳሌ መሆን እንደቻለ ይነገርለተል ፡፡ ይህ ለማነበት ጉዳይ ራስን የመስጠት ተፈጥሮው ዳብሮ ካደገ በኋላም በፃፋቸው Critiques of Pure Reason, Critiques of Practical reason, Prolegomena to any future Metaphysics  በመሳሰሉ ስራዎቹ ላይ ያሳየው ብስለት እጅግ በጣም ምጡቅ የሆኑ አሳቦችን ማካተት እንደቻለ መገንዘብ ይቻላል፡፡

image

የካንት ፍልስፍና
በፍልስፍና ታሪክ ከካነት በፊትና በካንት ዘመን  የነበሩ ሁለት የፍልስፍና ጎራዎች ከፍተኛ የሙሁራዊ ፍጭት ውስጥ የገበቡት ወቅት ነበር፡፡ አንደኛው ጎራ በዲካርቴስ፣ ሲፒኖዛና ሌቤንዝ ፊት አውራሪነት የሚመራው እና ትክክለኛ እውቀት ከሰው ልጅ ህሊና ውስጥ  ይመነጫል በሚል የሚከራከሩት በተለምዶ ራሽናሊስት (Rationalists) ተብለው የሚጠሩት ናቸው፡፡ በሌላው ጎራ እውቀት የሚገኘው ከሰው ልጅ ህሊና ውስጥ ሳይሆን በልምድ የሚገኙ ዉጫዊ ተሞክሮዎችን በማሰባሰብ በሚፈጠረው ግንዛቤ እውቀት በማደራጀት ነው የሚሉት እንደ ሁም፣ ሎክ ባርክሌይን የመሳሰሉ  እንግሊዛውያን ፈላስፋዎች የሚገኙበት ኤምፒሪስቶቹ (Empiricists)  ምድብ ነው፡፡ ካንት ታዲያ በፍልስፍናው የሁለቱን የሙሀራን ፍጭት እልባት ለመስጠት የሚያስችል አሳብ ለማቅረብ ጥረት አድርጓል፡፡ በሌላ በኩል ካንት ሀይማኖት በተለይም ክርስትና ከሳይንሱ ጋር የሚዛመድብትን መንገድ ለማመላከት ጥረት አድርጓል፡፡ የካንት ፍልስፍና ትንታኔ መንገድ በመሰረታዊነት ምክንያታዊ አሳቦችን በጥልቀት በማጥናት የሰው ልጅ ግንዛቤ የሚዳበርብትን መንገድ በተለይም ደግሞ በልምድ ሊገኙ የማይችሉ የተፈጥሮ እውነታዎችን ምክንያታዊ ትንታኔ በመስጠት እውቀት የሚዳብርበትን መንግድ መጠቆም ነበር፡፡ 

ሀ. ምጡቅ አሳባዊነት (Transcendental idealism)

ምጡቅ አሳባዊነት (Transcendental idealism) ካንት ለፍልስፍናው የሰጠው የዶክትሪን ስያሜ ሲሆን የሰው ልጆች በልምድ የሚያገኟቸው እውቀቶች በትክክል ነገሩን (a thing itself) የሚያንጸባርቁ ሳይሆን በምስል ደረጃ ግንዛቤ መፍጠር የቻሉትን ብቻ ነው የሚል ነው፡፡ እንደ ካንተ አሳብ ከሆነ ጊዜና ቦታ (Time and space) በትክክል ያሉ ቁሶች ሳይሆኑ አእምሮ ነገሮችን ለመረዳት የሚጠቀምባቸው የግንዛቤ ዉጤቶች ናቸው፡፡ በካንት አሳብ መሰረት የአእምሮ ግንዛቤየሚፈጥረው እውቀት የነገሮችን ባህሪያትን የሚመስል የውክልና ምስል እንጂ ትክክለኛ የነገሩን  (a thing itself) ትክክለኛ ባህሪያት የሚያመላክት አይደለም፡፡

በዚህ መሰረት ካንት የሰው ልጅ ስለማንኛውም ነገር የሚፈጥረውን  ግንዛቤ ሀ) የነገሩን ባህሪ በራሱ ይዘት በማጥናት የፈጠር  ግንዛቤ ጥናታዊ ግንዛቤ (analytic Judgement)  እና ለ)  በነገሩ ባህሪያት ላይ ተጨማሪ መረጃዎችን በመጨመር የሚገኝ ግንዛቤ ደግሞ ዉህድ ግንዛቤ (Synthetic Judgement) በሚል በሁለት ይከፍለዋል፡፡ ጥናታዊ ግንዛቤ (analytic Judgement) የሚባለው ነገርየው በራሱ የተዋሀደው መሰረታዊ ባህሪ ሲኖር ነው፡፡ ለምሳሌ “አበበ ረጅም ነው” የሚለው ጥናታዊ ግንዛቤ (analytic Judgement) ግንዛቤ ነው ምክንያቱም “ረጅም” የሚለው ባህሪ “ከአበበ” ጋር  የተጣበቀ ውስጣዊ ባህሪ በመሆኑ “ረጅም” የሚለውን ባህሪ መገንዘብ የሚቻለው የአበበን ቁመት በማየት ስለሚሆን ነው፡፡ በአንፃሩ የውህድ ግንዛቤ (Synthetic Judgement የሚፈጠረው በነገርየው ላይ ተጨማሪ ተቀፅላ ባህሪያትን በመጨመርና ከነገሩ ጋር በማዋሀድ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ “ቢጫ ሸሚዝ”  በሚለው አገላለፅ ውስጥ “ቢጫ” የሚለው ባህሪ ከነገሩ ጋር የውስጥ ዉህደት የለውም፡፡ በዚህ የተነሳ ከልምድ ተቀጥሎ የሚገባ ዉህድ ግንዛቤ ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ የግንዛቤ አይነት ባህሪው በነገሩ ውስጣዊ ይዘት ከሌለውና ተቀጥሎ የሚጨመር ባህሪ ከሆነ በዉህድ ግንዛቤ (Synthetic Judgment) ደረጃ ይወሰዳል፡፡

ለ. ክፍፍሎሽ ግንዛቤ (Categories of thought)

ለካንት  የሰው ልጅ ግንዛቤ የተለያዩ የተቆራረጡና የተበጣጠሱ ልምዶችን አንድ ላይ በማቀናጀትና በመዋሀድ ወጥ ግንዛቤን በመፍጠር የሚገለፅ ነው፡፡ ሂደቱም የሰው ልጅ አእምሮ በስሜት ህዋሳቱ በኩል ከልምድ የሚያገኛቸውን መረጃዎች ከጊዜና ቦታ (Time and space) ጋር በማደራጀት የተደራጀ የግንዛቤ ክፍል ይፈጠራል፡፡ ለካንት ጊዜና ቦታ (Time and space)  ማለት የራሳቸው ባህሪያት ያላቸው እውነታዎች ሳይሆኑ አእምሮ ነገሮችን ለመገንዘብ የሚጠቀምባቸው የግንዛቤ መፍጠሪያ የአሳብ ምስሎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ አእምሮ የሆነ ጠረጴዛን  ለመረዳት በመጀመሪያ ጠረጴዛው የያዘውን ቦታ እና ከጠረጴዛው ውጪ ያለውን ባዶ ቦታ በማስላት በጊዜ ሂደት ውስጥ በማገናዘብ ስለጠረጴዛው መሰረታዊ ባህሪ ይረዳል፡፡ በዚህ መሰረት በልምድ የሚገኙ መረጃዎች ከጊዜና ቦታ (Time and space) አንፃር እየታዩ የተለያዩ ክፍልፋይ አሳቦች ይይዛሉ፡፡ እነዚህ ክፍፍልፋይ አሳቦች በአንድ ላይ ይዋሀዱና ወጥ የሆነ ግንዛቤን ይፈጥራሉ ማለት ነው፡፡

ሐ የሚታይ እና የማይታዩ እውነት ( Phenomenal and Noumenal reality)

እንደ ካንተ እምነት የሰው ልጅ አእምሮ የመረዳት አቅሙ የተገደበ ስለሆነ ለመረዳት የማይችላቸው እውነቶች አሉ፡፡ ይሔ አሳቡ ደግሞ ካንትን እውነትን የሚታይ እና የማይታይ እውነት ( Phenomenal and Noumenal በሚል በሁለት እንዲከፍል አደረገው፡፡ ካንት የሚታይ እውነት ( Phenomenal በሚል ያስቀመጠው የሰው ልጅ በልምድ የሚያገኛቸውን መረጃዎች ተጠቅሞ የሚፈጥራቸው ግንዛቤዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ እኔ ስለ ጠረጴዛ የሚኖረኝ ግንዛቤ በዚህ ምድብ ሊመደብ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል የማይታይ እውነት ( Noumenal) የሚባለው እውነት ደግሞ ከአእምሮ ደካማ የመረዳት ችሎታ የተነሳ ከሰዉ ልጅ ግንዛቤ ዉጪ የሆነ እውነት ነው፡፡ ካንት እንደሚለው የሰው ልጅ አእምሮ በትክክል መረዳት ባለመቻሉ የተነሳ ከሰው ልጅ ግንዛቤ ዉጪ የሆኑ  የማይታዩ እውነታዎች ( Noumenal)   አሉ፡፡እነዚህም የእግዚአብሔር መኖር፣ ከሞት በኋላ ያለ ህይወት እና ነፃነት፡፡

Posted by EthioSophi Admin

Comments

Post a Comment

Popular posts from this blog

የፍቅር ፍልስፍና: ፍቅር ምንድነው?

የማካቬሌ ፍልስፍና

የፍቅር ትርጉሙ