" ቆም ብለን እናስብ!" የሚለው ማሰብ ማቆም

ትንሽ ጓደኝነት ላይ ዝርክርክ ስለሆንኩ እኔን የሚረዳኝ ሰው  እያጣሁ ተችግሬ አንድ ቀን " ቆሜ ማሰብ" ጀመርኩ ። ቆሜ የጠየቅኩት ጥያቄ እየሄደ " ከአንግዲህ ሰው በቃኝ" የሚል የቆመ መልስ ሰጠኝ። በመልሱ መቆም ስላልቻልኩ እየሄድኩ ማሰብ ስጀምር እኔን የሚረዳ  ሰው አገኘሁ።


ቆሜ ባሰብኩት የቆመ መፍትሄ "ሰው በቃኝ!" ብዬ ከሰው ጋር መኖር ማቆም ለኔ መፍትሄ አይደለም። ሰው ነኝ ከሰው ጋር መኖር አላቆምም። በአጋጣሚ በጓደኛዬ ፅሁፍ ላይ ስንወያይ ይሄ አሳብ መጣልኝ። ለማሰብ መቆም ያስፈለገው እየሄዱ ማሰብ አይቻልም?

image

ሀ) ማሰብን አለማሰብ

ህይወታችን ሁሉ የኩሬ ነው። የለውጥ ጅረት አይፈልግም። ሁሉም ተቋጥሮ መቆም አለበት። ራሳችን ችግር ስለሆንን በኩሬ ካልሆነ የሚፈታ ችግር የለንም። "የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል" ቅቤው ግን የእርጋታ ኩሬ  ሳይሆን የለውጥ መናጥ ነው። "የቆዬ ሰው ከሚስቱ ይወልዳል" ኢንቫሊድ! ከሚስቱ የሚወልደው በወሲብ የለውጥ ሂደት ነው። ይኼ ሁሉ "ከኩሬው ቆመን እናስብ" ለማለት ነው። ቆሞ ማሰብ ፣ ማሰብ ማቆም ነው። ለውጥ እየሄዱ በማሰብ መቆምን ከመሄድ ጋር  በማወዳደር ነው። ማሰብን ማሰብ። እነሱ ግን  ከቆምክበት ኩሬው እንዳትወጣ " ከድጡ ወደ ማጡ" ብለው ያስፈራሩሀል። ይሄ ካልሰራ ደግሞ " የማያውቁት አገር አይናፍቅም" ብለው እየሄድክ እንዳታስብ ያባብሉሀል። የማያውቀት አገር ካልናፈቀ፣ እኔም ካልሄድኩ የማውቀው አገር አይኖርም ማለት ነው። ካልሄድኩ አላውቀውም። ካላወቅኩት አልናፍቅም። ስለዚህ ለማሰብ የማሰብ ሂደት አስፈላጊ በመሆኑ ለማሰብ መራመድ እንጂ መቆም ግዴታ አይደለም።

ለ)  ኢምፕሊኬሽኑ

የአንድ አሳብ ጥንካሬ በነባራዊው ህይወት ተግባራዊ የመሆን አቅሙ ይል ነበር እንግሊዛዊው ፈላስፋ።  አውቄ ነው ራሴው ነኝ ያልኩት። ፈረንጅ ካልጠራሁ አታምኑኝም ብዬ ነው።

ቆሞ የማሰብ መርሀችን ችግር እያመጣ ነው። እንደ ማህበረሰብ በተረጋጋ ሰላም ውስጥ ሆነን የብሔርና የሀይማኖት ክፍፍል ውስጥ ሆነን በክላሽ የምንጠበቅበት ምክንያት  ቆመንም ማሰብ አለመቻላችንን የሚያሳይ እውነታ ነው። ቆመን የምናስበው አለማሰብን በመሆኑ በቆምንበት የአገር ችግር እንሆናለን። አንደኛው የለውጥ መንገዱን በድንጋይና በግንድ ይዘጋል። ሌላው ቆሞ እየነገደ ዋጋ ይጨምርና አገሩ ላይ ይቆማል። ባለፈው ረሀብ ሲያሯሩጠኝ የሆነ ግሮሰሪ የምትመስል ቤት ገብቼ ምሳ እንዳለ  ጠየቅኩ። መቼም የአቅሜን የሚመጣጠን ቤት አይቼ በመግባቴ ብዙ ሳልጨነቅ ዱለት አዘዝኩ። ዱለቷ ስትመጣ በባትሪ እየፈለግሁ፣ በዱለት ፍሬ እየቆጠርኩ በላሁና ሂሳብ ስል "አምሳ ብር!" ክው ልል አልኩና ተውኩት። መጨረሻ እንዲቀንሱልኝ ተከራክሬ እምቢ ሲሉኝ አንድ ጥያቄ ጠየቅኩኝ። " ቆይ!  25 ፍሬ ያላት ዱለት አምጥተህ አምሳ ብር የምከፍለው በአንድ የዱለት ፍሬ ሁለት ብር ነው እንዴ?" አበሻ የሚያሰበው ቆሞ ስለሆነ በራሱ በአገሩ ላይ የቆመ ችግር ነው። ነጋዴው ቆሞ ሲያስብ ዋጋ ይጨምርና ሸማች ይንጫጫል። ሌላው ቆሞ ባሰበው የመንግስት ሰራተኛ ቢቀጠር ሙሰኛ ይሆናል። አበሻ ቆሞ ሲያስብ በብሔርና በሀይማኖት ይከፋፈልና ይናቆራል። ተቃዋሚው ቆሞ ያስብና ትዝ የሚለው የአገር ጉዳይ ሳይሆን አብዮት ማስነሳት ነው። አንድ አበሻ ተቃዋሚ ለአገራዊ ችግር መፍትሄ ከአብዮት ውጪ ማሰብ ከቻለ ምክንያቱ ሁለት ነው። ወይ ተቃዋሚው አበሻ አይደለም። ወይ አበሻው ተቃዋሚ ሳይሆን የገዥው ፓርቲ አባል ነው። 

በኩሬ ውስጥ ሆነን ማሰባችን የሚፈጥረው ችግር የቆምንበት ኩሬ ላይ ችግር መፍጠር ብቻ ሳይሆን በእንቅስቃሴያችንም ላይ ችግር መፍጠሩ ነው። አበሻ ከኩሬው ውጪ ሌላ ውቅያኖስ እንዳለ ብታስተምረው እዛም ሄጄ ልቁም ነው የሚለው።  "ደቡብ አፍሪካ የምትገኘው በአህጉሪቱ በደቡብ በኩል ነው " ተብሎ ጂኦግራፊ ሲያስተምሩት አበሻ የሚማረው ደቡብ አፍሪካ ስለመሄድ ነው። አረብ አገር የሚሄዱ ሴቶች መብዛታቸውን ያዬ አንድ ጂኦግራፊ ቲቸር  የሴቶቹን ረጅም ሰልፍ አየና በቁጭት ምን ቢል ጥሩ ነው!? " ሳይቸግረኝ ኳታርና ኩዌትን አስተምሬ ስደተኛ ላብዛ!?" እሱ አገሯ ሰርታ ኳታርን እንድትፈጥር እንጂ ወደ ኳታር እንድትሰደድ አልነበረም ያስተማረው።  አበሻ ኩሬው ውስጥ ሆኖ የሚማረው ያለበትን ኩሬ ውቅያኖስ ስለማድረግ ሳይሆን ውቅያኖሱንም ኩሬ ለማድረግ ብቻ ነው። አንድ ጊዜ የሀይስኩል አስተማሪያችን ስለ ስዊዲን ህዝብ ስልጣኔ እያስረዳን ነበር። " ስዊድን በሞራል፣ በፖለቲካ የሰለጠኑ ህዝቦች ናቸው። እዛ ሌባ የለም።መስረቅ የለም። ሁሉም ታማኝ ነው።  ሂሳብ የሚጠይቅ የለም። " ብሎ ሲናገር አንዱ " እዛ ነበር መሄድ?" ብሎ ጠየቀ። ሌላው ምን ቢለው ጥሩ ነው!" እዚህም ሆነህ እኮ ሌባ አለመሆን ትችላለህ"! ችግር ለመቅረፍ ችግሩ የሌለበት ቦታ መሄድ አስፈላጊ አለመሆኑ ላይ ተነቃቁ። አሁንኮ ለአበሻ ኩሬን ለቆ መሄድ ችግር የለውም። ችግሩ ኩሬውን ለቆ ወደ ውቅያኖስ ሲገባ ማሰብ ያቆምና የሄደበት በራሱ ችግር ሆኖ ይቆማል።  አበሻ ኩሬውን ለመልቀቅ የሚንቀሳቀሰው ቆሞ የሚያስብበትን አለማሰብ ፍለጋ እንጂ እየተራመዱ ለመሄድ አይደለም። ቦታ ብንቀይርም አስተሳሰብ የማሰብ ለውጥ የለም። ተራመድን ከተባለ ቆሞ ማሰብ የሚችልበት ኩሬ መቀየር ነው። ያው ቆሞ ማሰቢያ ኩሬ ፍለጋ እንደኛ ስደተኛ የለም። ዘፋኙ፣ አርቲስቱ፣ ፀሀፊው፣ ሰአሊው፣ ከኩሬ ወደ ሌላ ኩሬ ይሰደዳል። አንዳንዱ እዛ ያለበት ኩሬ ሆኖ የለቀቀውን ኩሬ በፖለቲካ ትግል ስም ያምሳል። ሌላው ደግሞ እዚህ ያለነውን በየፈረንጁ አስፓልት ላይ " ኑኑ!" ይላል። አንዱ የአማረኛ ክሊፕ አየቶ የተናገረው "ኢትዮጵያዊ የሚሰደደው ክሊፕ ለመስራትና ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ብቻ ነው እንዴ!?" እንዳለው። እየሄዱ ማሰብ ካስተማረ መሰደድ እኮ ችግር የለውም። ችግሩ ስደትን የማቆም ቆሞ ማሰብ መሆኑ ነው። አሁንማ ተዋናዩ፣ ዘፋኙ ፣ ፀሀፊው ብቻ ሳይሆን ፓስተሩ  ፣ ቄሱ፣ ዘማሪው፣ ዳቆኑም  ሁሉም ወደ አሜሪካ መሰደድ ነው። እና አንዱ አዲስ አበባ የሚያውቃቸውን ፓስተሮች፣ አማሪዎች፣ ሰባኪዎች ጠቅላላ አሜሪካ ሲያገኛቸው በአግራሞት ምን ብሎ ቢጠይቅ ጥሩ ነው!?" ጀለሶች አገራችሁን ትታችሁ እዚህ የመጣችሁት እግዜር ሰፈር ቀየረ እንዴ?"  ከምር ዘፋኙ ጠቅላላ ወደዛ ሲሄድ ሙዚቃ ሰፈር የቀየረች ነው የሚመስለው። እዚህ ተዋናይና ዘፋኝ የምትጣራ ጥበብ እያለች ተዋናዩ ፣ ፀሀፊው ሲሰደድ  ጥበብ  ሰፈር የቀየረች ነው የሚመስለው። እግዜር የሚያስፈልገው ህዝብ ትቶ ፓስተርና ዘማሪ አሜሪካ ሲንጋጋ እግዜር ሰፈሩ ዲሲ ይመስላል።

እና ቆመን ባሰብነው ልክ ቆመናል። ቆመን ብንቀሳቀስም ለለውጥ ሳይሆን ተመልሶ ለመቆም ነው። ማሰባችን አለማሰብ በመሆኑ ከ3ሺ አመታት በኋላ መድረስ የቻልነው ያኔም የቆምንበት ቦታ ነው። ቆመን ማሰባችን ያቆመው እኛ እንጂ እየሄደ የሚያስበውን ለውጥ አይደለም። የቀድሞ የኢትዮጵያ መሪ አሁን ስልጣን ላይ ቢሆኑ ኖሮ በብስጭት ሊናገሩት የሚችሉት ንግግር ይህን ይመስል ነበር።
" ብታምኑም ባታምኑም ቆመናል። እየሄድን ቆመናል"

Comments

Popular posts from this blog

የፍቅር ፍልስፍና: ፍቅር ምንድነው?

የማካቬሌ ፍልስፍና

የፍቅር ትርጉሙ